በእውቁ ፖለቲካኛ አቶ ልደቱ አያሌው የቀረበ ጥሪ‼
Edited by : addiskignit@gmail.com -3/7/2023
ዶ/ር ለማ መገርሳን፣ አቶ ደመቀ መኮንንን፣ አቶ ገዱ አንዳርጋቸውን የመሳሰላችሁና “በቲም ለማ” ስም በለውጥ ሐዋሪያነት በህዝብ ስትሞገሱ የነበራችሁ ወገኖች - “ህይወታችንን ቁማር አስይዘን አመጣነው” ያላችሁት ለውጥ ከሽፎ ሀገሪቱ እናንተው ለስልጣን ባበቃችሁት መሪ እንዲህ ላለ አደጋ ስትጋለጥ የእናንተ ሚና በዝምታ አድፍጦ መኖር፣ ወይም የአገዛዙ ታዛዥና አገልጋይ መሆን ነበረበትን?” አቶ አዲሱ ለገሰን፣ አቶ ተፈራ ዋልዋን፣ ዶ/ር አርከበ ዕቁባይን፣ አቶ ኩማ ደመቅሳን፣ አቶ ህላዊ ዮሴፍን የመሳሰላችሁና የ17 ዓመቱ መራራ የትጥቅ ጥግል አካል የነበራችሁ ወገኖች - “ሙሉ የወጣትነት ዕድሜአችሁን በታጋይነት ያሳለፋችሁትና ብዙ ሺህ ጓዶቻችሁን በረሃ ላይ ቀብራችሁ የመጣችሁት ታገልንለት ያላችሁት ሀገርና ህዝብ እንዲህ በህልውና አደጋ ላይ ሲወድቅ የፖለቲካ ጡረተኛ ሆናችሁ በዝምታና በትዝብት ለማየት ነበርን?” ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስን፣ ፕሮፌሰር ብርሀኑ ነጋን፣ ዶ/ር አረጋዊ በርሄን፣ ዶ/ር በለጠ ሞላን የመሳሰላችሁ የተቃዋሚ ፓርቲ አመራር የሆናችሁና ሹመት ላይ የምትገኙ ወገኖች - “ለብዙ ዓመታት የደከማችሁበት የተቃውሞ ትግል የመጨረሻ ግብ የአምባገነን መሪ ሹመት ተቀብሎ የ አገዛዝ ስርዓት አጃቢና ተባባሪ ለመሆን ነበርን?” ክብርት ፕሬዚደንት ሣህለወርቅ ዘውዴን፣ ዶ/ር ዳንኤል በቀለን፣ ወ/ሮ መዓዛ አሸናፊን፣ ወ/ሪት ብርቱካን ሚደቅሳን፣ ፕሮፌሰር መስፍን አርዓያን፣ ዲያቆን ዳንኤል ክብረትን የመሳሰላችሁና ከፍተኛ የሞራል ልዕልናና የህዝብ አክብሮት ያተረፋችሁ ወገኖች - “የህይወት ዘመናችሁ የመጨረሻ ስኬት ከአምባገነን ስርዓት ሹመት ተቀብሎ የአገዛዝ መዋቢያ ጌጥ መሆን ነውን?” በ27 ዓመቱ የትግል እንቅስቃሴ የፓርቲ አመራር፣ አክቲቪስትና ጋዜጠኛ ሆናችሁ በግንባር ቀደምትነት ስትታገሉ የምናውቃችሁ አቶ አንዳርጋቸው ጽጌን፣ አርቲስት ታማኝ በየነን፣ አቶ አንዱዓለም አራጌንና አቶ የሺዋስ አሰፋን የመሳሰላችሁ ወገኖች - “የዛሬው አገዛዝ በሁለንተናዊ መልኩ ከትናንቱ አገዛዝ የባሰና የከፋ ሆኖ እያለ ዝምታን በመምረጥ ወይም ያልተገባ ሰበብ አስባብ በመስጠት ስርዓቱን ማባባል ወይም በለሆሳስ መደገፍ የመረጣችሁት ቀድሞውንም የትግላችሁ የመጨረሻ ግብ የስርዓት ለውጥ ሳይሆን የህወሐት መውደቅና የጠቅላይ ሚኒስትር ለውጥ ነበር ማለት ነውን?” በአጠቃላይ ከዚህ በላይ የተጠቀሳችሁ ወገኖችና በስራችሁ ስኬት የህዝብ አድናቆትንና ክብር ያተረፋችሁ ተዋቂ ስፖርተኞች፣ የኪነ ጥበብ ሰዎች፣ ጋዜጠኞች፣ ምሁራን፣ የሃይማኖት አባቶችና የሀገር ሽማግሌዎች፣ በተለያየ ደረጃ ሀገራችሁን ያገለገላችሁ የቀድሞ ባለስልጣናት፣ ወዘተ …ታዋቂና ባለዝና ብቻ ሳትሆኑ የሀገሩ ልሂቃንም ጭምር ናችሁና በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የህዝቡ መሪዎች የመሆን ኃላፊነት አለባችሁ። ዝናና ክብር ያለሀገርና ህዝብ ትርጉም የለውም። በሀገር መፍረስ ከሚመጣው አደጋም ማናችንም ተለይተን አንተርፍም። የወቅቱ ትግል ከፖለቲካ በላይ የሀገር ህልውና ጉዳይ መሆኑን በመገንዘብ ቢያንስ ስለአገዛዙ ያለንን ተቃውሞ በድፍረትና በጋራ ‘ጮክ ብለን…’ ልናሰማ ይገባል። በአንድ አምባ-ገነን መሪ ምክንያት ሀገር ሲፈርስ ዝም ብሎ ማየት “ባላገር” ነኝ ብሎ ከሚያምን ማንኛውም ዜጋ አይጠበቅምና የታሪክና የትውልድ ሃላፊነታችንን በጋራ እንወጣ። ልደቱ አያሌው የካቲት 25 ቀን 2015 ዓ.ም
test