የአለም አቀፍ ኢትዮጵያውያን ዲያስፖራ ግልፅ ደብዳቤ ለዶ/ር አብይ አህመድ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር
Edited by : addiskignit@gmail.com -3/9/2023
ዓለምአቀፍ የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ግልጽ ደብዳቤ ለዶ/ር ዓቢይ አህመድ አሊ፣ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚንስቴር አዲስ አበባ፣ ኢትዮጵያ የካቲት 29 ቀን 2015 ዓም (March 8, 2023) ለተከብሩ ዶ/ር ዓቢይ አህመድ ለኢትዮጵያ ሀገራችን ትውልድና ታሪክ ተሻጋሪ የሆነ ለውጥ ያመጣሉ በሚል ተስፋ የኢትዮጵያ ዳያስፖራ እርስዎንና መንግሥትዎን እስከዛሬ ድረስ በሙሉ ልብ ድጋፉን በመስጠት፤ ወደእናት ሀገሩ የእርዳታ ገንዘብ በመላክ፤ መዋዕለ ንዋዩን በማፍሰስ፤ በድርቅና በግጭት በመፈናቀል ብዙ ጉዳት የደረሰባቸዉን ዜጎቻችንን በመርዳትና መልሶ በማቋቋም፤ በኮቪድ ወረርሽኝ ወቅት በሞያ የተደገፈ ምክር በመስጠትና በቁሳቁስ በማገዝ ዳያስፖራው ለሀገሩ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አበርክቷል። ከእነዚህ በተረፈ፣ ለዐባይ የህዳሴ ግድብ ስኬት ገንዘብ በማዋጣትና በዲፕሎማሲው መስክ ድጋፍ በመስጠት ሰፊ የሆነ ያልተቋረጠ እገዛ አድርጓል። ሀገራችን ኢትዮጵያ በሰሜኑ የትግራይ ጦርነት ሳቢያ ከፍተኛ ውጥረት ውስጥ በገባችበት ወቅትም ዳያስፖራው ከእርስዎ፣ ከኢትዮጵያ ሕዝብ፣ ከመከላከያና የጸጥታ ኃይሎች ጎን በመቆም፣ ሀገራችንን ለማዳን በተደረገው ከፍተኛ እርብርብ፣ በተለይም በዓለም አቀፉ መስክ ግንባር ቀደም በመሆን በዲፕሎማሲና ሕዝብ ግንኙነት ዙሪያ ዳያስፖራው ያደረገውን ታላቅ ተጋድሎና አስተዋጽኦ ምንግዜም ታሪክ አይረሳዉም። በጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም. (Nov 4, 2020) ህወሐት በሰሜን እዝ ላይ ድንገተኛ ጥቃት በመክፈት፣ በሺህ የሚቆጠሩ ንጹሀንን በተኙበት ሳይቀር ጨፍጭፎ፣ በአማራና አፋር ክልሎችም በዘመተበት ወቅት፣ ኢትዮጵያ በታሪኳ አይታው የማታውቀው የዲፕሎማቲክ ዘመቻ፣ የኢኮኖሚ ማዕቀብ እና ከምዕራባውያን እና የአለም አቀፍ ሚዲያዎች ከፍተኛ ጫና ገጥሟት ነበር። ይህን ለመቋቋም በዓለም ዙሪያ ያለው የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ከጫፍ እስከጫፍ በመነሳትና በየሲቪክ ማህበሮቻችን በመደራጀት፣ ከፍተኛ የሆነ የዲፕሎማቲክ እንቅስቃሴ አድርገን፣ የጥብቅና ዘመቻዎችን በማደራጀት፣ ዲፕሎማሲያዊ ድጋፍ በመስጠት፣ በተለይም የዩናይትድ ስቴትስ ኮንግረስን፣ የተባበሩት መንግስታት ድርጅትን እና ሌሎች አለም አቀፍ አካላትን ሎቢ በማድረግ ታላላቅ የዲፕሎማሲ ስኬቶችን አስመዝግበናል። በተጨማሪም ከሰላም ደጋፊ “ፓን-አፍሪካን” አጋሮቻችን ጋር በመተባበርና፤ ትግላችንን በማቀናጀት የ“#በቃ” (#NOMORE) ሰፊና ሕዝባዊ ንቅናቄ በዓለም ዙሪያ የህወሐትን የሀሰት ፕሮፓጋንዳ በማክሸፍ፤ የኢትዮጵያ ችግር የአፍሪካ ሁሉ ችግሩ ሆኖ እንዲታይ፤ የምዕራብ አለም ዜጎች አብረውን እንዲቆሙና ድምጽ እንዲሆኑ ታላቅ አስተዋጽዎ አድርገናል። በአምስት አህጉራትና ከሰላሳ ሁለት በላይ አገሮች ውስጥ ታሪካዊ ታላላቅ ሰለማዊ ሰልፎችን በማድረግ፣ ኢትዮጵያ በአለም አደባባይ የተነፈገችውን ትኩረት ድምጽ ልንሆንላት ችለናል። እኛ፥ ከእዚህ ደብዳቤ በታች የፈረምነው ዓለም አቀፍ የዳያስፖራ ድርጅቶች፣ ግንባር ቀደም መሪ በመሆን ሌትና ቀን ያለእረፍት በመታገል፤ ለሀገራችን ኢትዮጵያ በምንችለው ሁሉ አቅም፣ በእዉቀት፣ በሞያ፣ በገንዘብ፣ በጉልበትና በጊዜ ከፍተኛ መስዋእትነትን የከፈልን ነን። በከፍተኛ ሀገር ፍቅር ስሜትም ተነሳስተን ይህን አስተዋጽኦ ለማበርከት በመቻላችን ልዩ ኩራት ይሰማናል። ይሁን እንጂ፣ ይህን ስናደርግ የእርስዎን “የብልጽግና ፓርቲ” አጠራጣሪ ታሪክ ማለትም፤ የህወሐትን (ኢህአደግ) ጠባብ የብሄር፣ የዘረኝነትና ከፋፋይ የፖለቲካ መስመርና፣ በሕዝብ ላይ የፈጸመውን ግፍና ደባ ለአፍታም ቢሆን በመርሳት አይደለም። ያንን ሁሉ በሆዳችን ይዘን፤ ሀገራችን ኢትዮጵያን ወደላይ ከፍ በማድረግ፤ ለሕዝባችን ነጻነት፣ ፍትሕ፣ እኩልነትና ብልጽግና የሰፈነበት ስርአት እንዲገነባ “እናሻግራታለን” ያሉንን ቃል ኪዳን ተስፋ በማድረግና በማመን ነበር ከጎንዎ የቆምነው። ይሄም በብዙዎች ዘንድ መደገፍ የማይገባውን ስርአት እንደደገፍን አስቆጥሮን ነበር። አሁን እርስዎና መንግሥትዎ በሕዝብ ላይ የሚያደርሱትን በደልና ግፍ ስናስተዉል ግን፤ እኛም ከሕዝባችን ጋር አብረን የተከዳን አይነት ስሜትና ቁጭት ነው የሚሰማን። በሚያሳዝን ሁኔታ፣ ለኢትዮጵያ ሕዝብ ቃል ገብተው ባፈረሱት ቃል ኪዳን የተነሳ፣ በእርስዎ አመራር ላይ ያለን እምነት ከምንጊዜውም በበለጠ አዘቅት ወርዷል። ሀቁ እንደሚያሳየው፣ እርስዎ ከአምስት አመት በላይ በመንግሥት ሥልጣን መሪነት በቆዩባቸው አመታት ውስጥ፣ ሀገራችን ኢትዮጵያ እጅግ በሚዘገንን ሁኔታ ላይ ትገኛለች፤ በሺዎች የሚቆጠሩ ንጹሀን ዜጎች ተጨፍጭፈዋል፤ በሚልዮን የሚቆጠሩ ተፈናቅለዋል፤ የሕዝቡ ሰብአዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች ከምንጊዜዉም በበለጠ ተጥሰዋል፤ መንግሥት እራሱ ህገ መንግሥቱን አያከብርም፤ የህግ የበላይነትና ተጠያቂነት የሚባሉት በሀገሪቱ ስማቸውም ተረስቷል፤ ሌብነትና ሙስና የኑሮ ውድነት ሕዝቡን አስመርሮታል፤ በሚልዮን የሚቆጠሩ ንጹሀን ዜጎች ለረሀብና ለስደት ተጋልጠዋል፤ ችግሩ ተዘርዝሮ አያልቅም! ከእዚህ በታች ዋና ዋና የሚያሳስቡንን፤ ለሀገራችን ሠላም፣ ለሕዝባችን ደህንነትና ለህልውናዋ የሚያስጨንቁንንና፤ ሌትና ቀን ቁጭት የሚያሳድሩብንን ክስተቶች ለመዘርዘር እንሞክራለን፥ በሚዘገንን ሁኔታ እያየን ያለነው መግታት ያቃተዎት የሰብአዊ መብቶች መጣስ እጅግ አድርጎ ያሳስበናል፤ በእርስዎ አመራር ስር በዘር እየተለየ የሕዝባችን በገፍ መታሰርና መንገላታት፤ በጠራራ ጸሀይ መገደል፤ የመናገር፣ የመጻፍ፣ የመሰብሰብና ሰላማዊ ሰልፍ የማድረግ፤ የማምለክ ነጻነት መገፈፍ፤ በነጻ ከቦታ ቦታ የመንቀሳቀስ መብቶች ወዘተ መቆም፤ ከባድ የሆኑ በሰው ልጅ ላይ እየተፈጸሙ ያሉ ወንጀሎች፤ ከመጠን በላይ ብቻ ሳይሆኑ፣ መንግስትዎ እያወቀ መሆናቸው፤ ጋዜጠኞች እና የሰብአዊ መብት ተሟጋቾችን ጨምሮ የተቃውሞ ድምጽ ያሰሙ ወይም የአገዛዙን ፖሊሲዎች የሚቃወሙ ታስረዋል። በመላው ኢትዮጵያ በግፍ የታሰሩ የህሊና እስረኞች ቁጥር፣ ከመብዛታችው የተነሳ፣ ይህ ነው ለማለት አዳጋች ነው፤ ሕዝቡ በእርስዎ አስተዳደር ላይ ተስፋ እየቆረጠ ነው፤ ሌላዉ ቀርቶ፣ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትን ወደጎን በመተው፣ ተቃዋሚ የሚባሉትን ጥቂት ድምጾች፥ ለስሙ እንኳን ሳያዳምጡ በአንገብጋቢ የሀገር ጉዳዮች ላይ እንደፈለጉ በግልዎ ዉሳኔ ይሰጣሉ፤ ህወሓት የፕሪቶሪያን የሰላም ስምምነት በግልፅ እየጣሰ የእርስዎ አስተዳደር የህወሀትን ወንጀለኛ ድርጅት መልሶ ለማቋቋም በትጋት ሲሰራ በከፍተኛ ስጋት እየተመለከትን ነው፤ ይህን ሁሉ ዓመት በኦሮሚያ ክልል በሰላማዊ ሕዝብ፤ በተለይም ዘራቸው እየተለየ በአማራ ዜጎች ላይ የሚደርሰዉን አስከፊ ጭፍጨፋ ለማስቆም ባለመቻልዎ፤ እንዲሁም የኦሮሞ ብልጽግና አባላትና የመንግስት ባለስልጣኖች በሀገሪቱ ፓርላማ “አሸባሪ” ተብሎ ከተሰየመው “ኦነግ ሠራዊት” ጋር መነካካታቸውን እያወቁ ባለማስቆምዎ እጅጉን አዝነናል፤ በሰዉ ልጆች ላይ አሰቃቂ ወንጀል ሲፈጸም፤ በደቦ ድብደባና ግድያ፤ ሴቶችን እናቶችንና ህጻኖችን መድፈር፤ ከእርጉዞች ጽንስ በሳንጃ እያወጡ ማረድ፤ ወንዶችን አንገታቸዉን መቅላት፣በአንድ ቤት ውስጥ በማጎር በእሳት በማጋየት፣እና ሌሎችንም ለጆሮ የሚዘገንንኑ ወንጀሎች እያዩ፣ ይህን ያህል ዓመት ድንግጥ ብለው በማዘን፤ የመንግሥትዎን ኃይል ከሕዝብ ጋር አስተባብሮ በጋራ በመጠቀም እንዳይቀጥል ማስቆም አለመቻልዎ፤ በተለይም በአማራ ኢትዮጵያውያንና የኦርቶዶክስ እምነት ተከታዮች፤ እንዲሁም በሌሎች ብሄረሰቦች በጉራጌና ጌዲኦ፣ እንዲሁም በሻሸመኔ ኗሪዎችና በመሳሰሉት የደረሰዉን ግፍ አለማስቆምዎና፤ ወንጀለኞችንም ለፍርድ ማቅረብ አለመቻልዎ፤ በምእራብ ኦሮሚያ (ወለጋ) በተለይ በደርግ ዘመን፣ 1970ዎቹ በተደረገው የድርቅ ሰፈራ ከሰሜን የመጡ አማራ ዜጎች ላይ እየተካሄደ ባለው የዘር ማጥፋት ወንጀልና ጭፍጨፋ ማንንም በህግ ተጠያቂ በማያደርግ መልኩ አሁንም እየቀጠለ በመሆኑ፤ በተለይም የክልሉ አስተዳደርና ፖሊስ፤ ወንጀለኞች ይህን የተደራጀ የዘር-ማጥፋት ግፍ ሲፈጽሙ ድንገት እንደተቀሰቀሰ የጎሳ ግጭት አድርጎ፣ አይቶ እንዳላየ ማለፍ፣ ወይንም ለሚያደርጉት ትብብር በኢትዮጵያና በዓለም ዙሪያ ያሉ የሰብአዊ መብት ተሟጋች ኃይሎችን እጅግ አስቆጥቷል፤ ህገ መንግሥቱን በመጣስ፤ የእርስዎ መንግሥት በተደጋጋሚ በኃይማኖት ጣልቃ እየገባና ፖለቲካ እየሰነቀረ፤ ብዙ ጉዳት እያደረሰና የሀገራችንን ሰላምና አንድነት በማናጋት ለህልውናዋም አስጊ እየሆነ በመምጣትና የኃይማኖት አባቶችንም መናቅና ማሰቃየት፤ በተለይ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የእርስዎ መንግሥት ኢላማ ለመሆኑ፤ በቅርቡ መንግሥት በኃይማኖት ላይ ጣልቃ በመግባቱ ሳቢያ ሲኖዶሱን ለሁለት በመክፈል፣ በሀገሪቱ አንዣቦ የነበረዉ አደጋና፤ በሕገወጥ በተሾሙ ጳጳሳት ምክንያት በሻሸመኔ የኦርቶዶክስ ምእመናን ላይ የተደረገው ጭፍጨፋ፤ እንዲሁም በቅርቡ የአድዋን ድልንና የቅዱስ ጊዮርጊስን በዓላት ለማክበር በወጡት ምእመናን ላይ የደረሰው ድብደባና ግድያ፤ በአስለቃሽ ጭስ መታፈን በቂ ምስክሮች ናቸው፤ ገና ዉጤቱ ያልታየዉንና ስኬቱ የሚያጠራጥረዉን “የብሄራዊ ምክክር ኮሚሽን” ከማቋቋም ባለፈ፣ መንግሥትዎ እስካሁን ድረስ በቅንነትና በቆራጥነት ተነሳስቶ፣ በህወሐት-ኢህአደግ የተመሠረተዉንና በብሄር ፖለቲካ ላይ የቆመዉን የዘረኝነት ሥርአትና፣ ህገ መንግሥቱን ለማሻሻል ወይም ለመቀየር ይህ ነው የሚባል እርምጃ ሲወስድ አይታይም፤ ከ3.6 ሚልዮን ዜጎች በላይ ከቀያቸው መፈናቀል፣ ኢትዮጵያን በሀገራቸው-ዉስጥ በተፈናቀሉ ዜጎች ቁጥር ከዓለም አንደኛ አድርጓታል፤ የከተሞች ልማት በሚል ሰበብ፤ በአዲስ አበባ ዙሪያ ለአመታት የኖሩ በሺዎች የሚቆጠሩ ኦሮምኛ የማይናገሩ ዜጎችን፤ ያለምንም ማስጠንቀቂያ በማንነታቸው እየተለዩ ቤታቸውን በሌሊት በላያቸው ላይ በቡልዶዘር እያስፈረሱ፣ ህጻናትን፣ ሴቶችንና አዛዉንትን ለረሀብ፤ ለስደትና ለአዉሬ ሳይቀር መዳረግ ከፍተኛ የሆነ ኢሰብአዊ ግፍና ወንጀል ነው፤ አስተዳደርዎ ህገ መንግሥቱን ኢፍትሐዊ በሆነና በዘፈቀደ መንገድ እንደሚተገብር በበርካታ ምሳሌዎች ማስረዳት ይቻላል፤ ከእነዚህም በቅርቡ፤ በደቡብ ኢትዮጵያ ለአንድ ብሄረሰብ (ሲዳማ) አዲስ ብሄርን መሰረት ያደረገ ክልል ሲፈጠር፣ በተመሳሳይ መልኩ ለሌሎች ብሄረሰቦች፤ ለምሳሌ እንደጉራጌ እና ወላይታ ያሉት ግን መከልከል ብቻ ሳይሆን መብታቸዉን ለማስከበር ሰላማዊ ሰልፍ እንኳን እንዳያደርጉና ድምጻቸዉን እንዳያሰሙ እየታፈኑ፤ ለእስርና ለድብደባ ለእንግልት ተዳርገዋል፤ ሌላዉ ቀርቶ የመጠጥ ውሀ ለወራት በማጣት ጉዳት ደርሶብናል በሚል ድምጻቸዉን ለማሰማት በወልቂጤ ባዶ ጀሪካን በትከሻቸው ይዘው ለሰላማዊ ሰልፍ የወጡትን ንጹሀን ዜጎችና በሻሸመኔ ወደ ቤተ ክርስቲያን ለጸሎት የሄዱትን ዜጎች የጸጥታ ኃይሎች በግፍ ገድለዋል፤ እንደተለመደው ለጥያቄና ለፍርድም አልቀረቡም፤ እርስዎ የሚመሩት መንግሥት፤ ዓለም የሚያደንቃቸውን የሀገራችንን የረዥም ጊዜ ታሪኮችና ቅርሳቅርሶች እንደፈለገው እየበረዘ ደብዛቸዉን ማጥፋት፤ ብሄራዊ አርማዎችን፣ የባህል ተቋሞችንና፣ የጥንት ቅርሶችን ማፍረስ፤ በኅብረ ብሔርዊነት የሚታወቁ ትልልቅ ከተሞችን ወደ አንድ ብሔር የበላይነት መቀየር፣ ከኢትዮጵያዊነት ወደዘርና ጎሳ ደረጃ ማዉረድን ተያይዞታል፤ ለኢትዮጵያዉያን ብቻ ሳይሆን ለአፍሪካ ታላቅ ኩራት የሆነዉ የአድዋ ድል በዓል እየደረሰበት ያለው ፈተና ለእዚህ ጥሩ ምሳሌ ሊሆን ይችላል፤ አስተዳደርዎ ከመድብለ ባህላዊነት ይልቅ በአንድ የጎሳ የባህል-አብዮት ላይ አተኩሯል። የኢትዮጵያ መዲና እና የአፍሪካ ዲፕሎማሲያዊ ማዕከል የሆነችውን የአዲስ አበባ ባለቤትነት ከአህጉራዊ እና አገራዊ ቦታዎ ዘቅጦ የአንድ ጎሳ የበላይነት ለመውሰድ የሚደረገው ጥረት አሳፋሪ ብቻ ሳይሆን፣ ማለቂያ ወደሌለው ደም መፋሰስና እልቂት ሀገራችንን እንድታመራ እያደረጋት ነው፤ አባቶቻችን ምንም አይነት የዘርና ሀይማኖት የጎጥ ልዩነት ሳያግዳቸው፤ ሀገራቸዉን ከጠላት ለማዳን ለነጻነቷ ሲዋደቁና በህይወታቸው መስዋእትነትን ሲከፍሉ፤ የአፍሪካ ሀገራትም ከቅኝ ግዛት ነጻ ለመዉጣት ሲታገሉ በኩራት ያነገቡትን አርማ፤ አርንጓዴ ቢጫ ቀይ ህብር የተላበሰዉን የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ አታሳዩን እያሉ የመንግሥት ጸጥታ አስከባሪዎች ዜጎችን ሲያስሩና ሲደበድቡ ምንም ሳይባሉ ሲቀሩ፤ አሁን ጭራሽ የአድዋን ድልም በምኒልክ አደባባይ ልታከብሩ አትችሉም መባሉ እጅግ አሳዛኝ የታሪክ ጠባሳ ሆኖአል፤ በየካቲት 23 ቀን 2023 ዓም የአድዋ የድል በዓል በሚከበርበት እለት፤ የመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች ታሪካዊዉን የቅዱስ ጊዮርጊስ ኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ግቢ በጉልበት ገፍተው ገብተው፤ በዓሉን በጸሎትና በወረብ በሚያከብሩት ካህናትና ምእመናን ላይ በድንገት በአስለቃሽ ጭስ ተኩስ ከፍተው፣ በብዙዎች ላይ ከባድ የመቁሰል ጉዳት ማድረሳቸው፤ በዚህም ዕለት ለበዓሉ የወጡ ንጹሐን ዜጎች በጥይት ተኩሶ በመግደል፣ በጭካኔ እንደ አራዊት በመደብደብ ይህ በሰላማዊ ዜጎች ላይ የተደረገው ግፍ፤ በሀገራችን ኢትዮጵያ ምን ያክል ፍትሕና የህግ የበላይነት እንደጠፋና፤ የፖሊስ አምባገነን አስተዳደር እየገነነ እንደመጣ በግልጽ የሚያሳይ ነው፤ ባለፉት አምስት አመታት በእርስዎና የመንግሥትዎ አገዛዝ ወቅት የሀገራችን ወሰንና ዳር ድንበር በተዳጋጋሚ ጊዜ እየተደፈረ ነው። በተለይም በሱዳንና ደቡብ ሱዳን አዋሳኝ ቦታዎች የመንግሥትና የሌሎች ኃይሎች ከጎረቤት ሀገር እየገቡ፤ ኢትዮጵያዉያንን ማጥቃት እየተለመደ ሄዷአል። በዚህም በርካታ ዜጎቻችን በየጊዜው ህይወታቸው ያልፋል፤ ንብረታቸው ይዘረፋል፤ ከቀያቸው እንዲፈናቀሉም ይደረጋል፤ የሀገራችን መሬትም እየተቀማ ለባዕድ ሀገራት መጠቀሚያ ሲሆን መንግስትዎ ዝም ብሎ ማየትን መርጦአል፤ ልክ ከእርስዎ በፊት እንደነበሩት መንግሥታት የእርስዎም አስተዳደር ለዜጎቹ የምግብ ዋስትና ለማምጣት እስከዛሬ አልቻለም፤ እንደ ተባበሩት መንግሥታት የሰባዊ እርዳታ ጉዳይ አስተባባሪ ቢሮ (OCHA) መረጃ ከሆነ ከ20 ሚልዮን በላይ የሚሆኑ ኢትዮጵያዉያን በህይወት ለመኖር ዛሬ የምግብ እርዳታ ያስፈልጋቸዋል፤ የቅርቡ በረሀብ ተጎጅዎች ደግሞ በኦሮሚያ ክልል ዉስጥ በቦረና የሚኖሩት ኢትዮጵያዉያን ናቸው። ይህ ሁሉ ከባድ የረሀብ አደጋ በሀገራችን እያንዣበበ እያለ፤ እርስዎ ግን የአስተዳደርዎን “መልካም ገጽታ” ለመገንባት ሲሉ የስንዴ ምርት ወደዉጭ ሀገር ለመላክ፣ አንድን ጎሳ በዋስትና ለመሸንገል፣ ሽርጉድ ይላሉ፤ በመንግስት ውስጥ የተንሰራፋው ሙስና፤ የዋጋ ግሽበት እና ወገንተኝነት እጅግ አሳሳቢ ደረጃ ላይ እየደረሰ ሲሆን፤ የእርስዎ መንግሥት ምን ያክል ማስተዳደር እንዳቃተው ቁልጭ አድርገው ያሳያሉ፤ ለእነዚህና ሌሎች ዘርፈ-ብዙ ተግዳራቶች ከቀን ወደቀን እያደጉ ለመጡ የሀገሪቱ ዉስብስብ ችግሮች መፍትሄ ለመሻት ቁርጠኝነት ባለማሳየትዎ፤ በተለይም የፌደራልና የኦሮሚያ ክልል የጸጥታና አስተዳደር አካሎች ግፍ ሲፈጽሙ እያዩ እንዳላዩ፤ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ ድጋፍ በማሳየትዎ፤ በኢትዮጵያ የስርአት አልበኝነት ባህል እንዲነግስና፤ የህግ የበላይነትና ፍትሕ እንዲጠፉ በሩን ከፍቷል። ለምን እና በማን ስልጣን እንደዚህ አይነት ችግር ያለባቸው ፖሊሲዎች አገሪቱ ተከተለች ለሚለው ጥያቄ ሃላፊነት በእርሶ ላይ ነው - የሀገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር፣ የመንግስት ርዕሰ መስተዳድር እና የጦር ኃይሎች ጠቅላይ አዛዥ እርስዎ ስለሆኑ። አሁንም በቆራጥነትና በቅንነት ተነሳስተው፤ በማስተዋል ወሳኝ የሆኑ መፍትሄዎችን መውሰድና በቶሎ በሥራ ላይ ማዋል ካልቻሉ፤ በዓለም ላይ እራሷን ለማጥፋት የምትጓዝ ብቸኛ ሀገር ኢትዮጵያ ትሆናለች። ያኔ እርስዎና መንግሥትዎ በታሪክ ተወቃሽ ይሆናሉ። ስለዚህ የኢትዮጵያ ዲያስፖራ ድምፅ ለሌለው የኢትዮጵያ ሕዝብ ድምጽ የመሆን ግዴታ አለበት። ለኢትዮጵያ ሕዝብ ቃል የገቡትን ለማክበር፣ የአገዛዝዎ ብልሹ አሰራርን ማስተካከያ እድሉ አሁን ነው። ይህንን አደገኛ አካሄድ በአስቸኳይ ለመቀየር እና ጥፋቶችን ለማረም፣ ዜጎችን ለመጠበቅ እና ቅሬታዎችን ለመፍታት ቆራጥ የማስተካከያ እርምጃዎች እንዲወስዱ እንጠይቃለን። ዛሬ የመንግሥት መቀጠል ብቻ ሳይሆን፤ የኢትዮጵያ እንደ ሀገር የመቀጠል ህልውና አደጋ ላይ ነው ያለው። አስተዳደርዎ ኢትዮጵያን ከአስገባት ከዚህ አጣብቂኝ ጨለማ ለማውጣት እድሉ በእጅዎ ነው። በሰከነና በእውነት መንፈስ የሚወሰዱ እርምጃዎች ሁሉንም ኢትዮጵያዊ ባለድርሻ አካላት አሳትፎ ሀገራችንን ለማዳን በአስቸኳይ ስራ እንዲጀመር አጥብቀን እናሳስባለን። ፈጣሪ ኢትዮጵያንና ልጆቿን ይባርክ!!!
test