“የኛ ነው እኮ . . .የኛው ነው እራሱ” - ሶስና አሸናፊ
Edited by : addiskignit@gmail.com -3/11/2023
...አልጣሽ አልታየ እባላለሁ፡፡ አልታየ አጎቴም አባቴም ነው፡፡ ንፍጤን እየጠረገ አሣድጎኛል፡፡ እንደኔው ከእለታት አንድ ቀን ከሀገሩ ድንገት ወጥቶ የቀረ፡፡ ጨርቄን ማቄን ርስቴን ከብቴን ሣይል ብን ብሎ የጠፋ ፡፡ ከዚያች ከደሣሣ ጎጆው፡፡ እኔም እንደሱ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ሀገሬን ትቻት ስወጣ እንደዛሬዋ አይነት ፀሃይ እያቃጠለች ነበር የሸኘችኝ፡፡ ከዛሬዋ ፀሃይ ውስጥ ደግሞ ያለከልካይ የሚወርደው ብርድ ይለበልባል፡፡
ከአንድ ሠማይ ስር ሁለት ፀሃይ፤ አንድ አለም.. . አንድ ፈጣሪ.. . .
ሣቄ አመለጠኝ፡፡
አባት ፣ እናት ፣ ወንድም አጎት ጎረቤት ፍቅረኛ . . . ኡሁ ጊዜ ደጉ ያፅናናል፡፡
ንፍጤ ይዝረበረባል ፡፡ አጎቴ አላየ፡፡ በቅዝቃዜው የሚወርድ እንባዬን መጥረግ አቅቶኛል፡፡ ያኔም እንዲህ ነበር፡፡ ከሀገር ስወጣ ላቤ በጆሮ ግንዴ እየወረደ ጭንቅላቴ በላብ ይጨስ ነበር፡፡ ሞኝ አይደለሁ አጎቴን ልፈልግ ነበር ከሀገር አወጣጤ፡፡ አቅም ያለኝ መስሎኝ ምን ሆኖ ነው ብዬ. . . ደግ አይሉኝ ክፉ ወይም ትልቅ አይሉኝ ትንሽ ብቻ እራሴ ለራሴ እንዳሰብኩ እዚህ ደረስኩ ፡፡ ይኸው እንቀዋለላለሁ፡፡ ያሰብኩት አልሆነም ፡፡ ብጠጣ ባልጠጣ ማን ጠያቂ አለኝ ፡፡መሸ ነጋ ሄደ መጣ ግድ የለኝም፡፡ ፀጉሬ ተበጠረ ተንጨባረረ ጉዳይም እይሰጠኝ፡፡ ውይ መጠጥ ባይኖርልኝ ይሄኔ ባቡር ስር ነበርኩ፡፡ አጎቴ ምስኪን ቩልክ ብሎ ወጥቶ ሹልክ ብሎ ሲቀር አገኘዋለሁ ብዬ ተከተልኩት፡፡ ማን ያውቃል በሱ ዝምተኛነት ይሄንን ጭራቅ አለም እንዴት እንደተጋፈጠው? ዝምተኛ ነበር፡፡ ለምን በሱ ስም እንደጠሩኝ አላውቅም ፡፡ ስለወላጆቼ ጠይቄም አላውቅም፡፡ እንድጠይቅም እድል አልተሰጠኝም፡፡ እነሱም አላወሩልኝም፡፡ ለምን ከነሱ እንደተፈጠርኩም አላውቅም፡፡ ብቻ አባቴም አጎቴም አቶ አልታየ ስለሆነ ጠገበች አልጠገበች ፣ ተመቻት አልተመቻት ፣ከፋት ደስ አላት የሚለኝ እሱ ነበር ፡፡ ድንገት ተለየኝ፡፡ የሚገርመው ሰው ከሰው ሣይሆን ሰው ከራሱም እንዴት እንደሚለይ የሚያውቀው ቆይቶ ብዙ ነገሮችን ከአጣ ወይም ከጠፋበት በኋላ መሆኑን ማንም አያውቀውም ፡፡ አሁንማ እድሜ ለሀገሩ ወይም ለሰው ወይም ለሁኔታው ወይም ለኔው ለራሴው እንኳን አጎቴን እራሴን አጥቼዋለሁ፡፡
የዛሬው ብርድ ጂኔን ከቦርሣዬ እስካወጣ እንኳን ጊዜ አልሰጠኝም፡፡ የእጄ ጣቶች በቆፈኑ አልንቀሣቀስ ብለው ተቆልምመዋል፡፡ እንደሁል ጊዜው ብርዱን ለማምለጥ አሮጌ ልብስ መሸጫ ሱቅ ጥልቅ አልኩ፡፡ የውስጥ ሙቀት እጁን ዘርግቶ ተቀበለኝ፡፡
ሠው ጨረቃ መስሏል፡፡
ለምግብ እንጂ ለጨርቅ እንዲህ ሰው ሲተራመስ አላየሁም፡፡ መቼም በነፃ የቀረበ ምግብ ያስፈነጥዛቸዋል፡፡ በቅናሽ የሚገኝ እቃም እንዲሁ፡፡
ፅድቅና ኩነኔ ያለበት ሀገር
የቤቱን ሙቀት እያመሠገንኩ ለመራመድ አንድ እግሬን ሣነሣ አንዱ ጀርባዬን መቶኝ ከፊት ለፊቴ ወለሉ ላይ ተዘርጋ ፡፡ በጭቃ ይሁን በጭቅቅት የተርመጠመጠው አላውቅም ሠውነቱ በክቷል፡፡ ሰውነቴን ገረመምኩት ፡፡ መቼ እንደታጠብኩ ጠፍቶብኛል፡፡ ሰውየው ግን ረጅም አይሉት አጭር ኮት እላዩ ላይ ጣል አድርጓል፡፡ በጀርባው ተንጋሎ ሲንፈራገጥ ሲያዩት ገበያተኛው በድንጋጤ ጨኸ ፡፡ ሠራተኞቹ ከያሉበት መተው ሠውየውን ከበቡት ፡፡
“አራበኝም . . ሠላማዊ ነኝ ግን ልብስ ስጡኝ ፣ ጫማ ፣ ቀበቶ ፣ ካልሲ ብርድልብስ በረደኝ “ እያለ ከሚንገጫገጨው ጥርሶቹ መሀል እየተቆራረጠ የሚወጣው ድምፅ አየሩ ላይ ተበተነ፡፡
እንባው በቅዝቃዜ ከደረቁ ጉንጮቹ ላይ ብቻውን ይንከባለላል፡፡ በለበሰው ኮት ውስጥ ገብቼ ማቀፍ እና ማሞቅ አማረኝ ፡፡ ሰውዬውን ጉዳት ከእድሜው ጋር ተጨምሮ አጎሣቁሎታል፡፡ ጫማ በእግሩ የዞረ እስከማይመስል የውስጥ እግሩ ቆስሏል፡፡
ሆዴ ክፉኛ ተረበሸ፡፡
“ማንም የለኝም ማንም “ ድምጹ ደጋግሞ ጆሮዬ ላይ አንቃጨለ . . ዛሬ ነገ አገኘዋለሁ ብዬ ተስፋ የማደርገው አጎቴ ም እንዴት እንደሆነ ማየት ናፍቆኛል ?
ከራሴ ጋር ሙግት ገጠምኩ ፡፡ ሰው መሀል በብርድ ከሚጠበስ እቅፍ አድርጌ ባሞቀው አልኩኝ፡፡
“ኧረ ምን በወጣሽ” አለችኝ ቀይ ወፍራም ረዥም ሴት ፡፡ ለካ ቃሉ ከአፌ አምልጧል፡፡
“ውይ ሲሞት በድኑን ከበን እንውል የለም” አለኳት
“ይኸው እንካ “ አለ እላዩ ላይ ስስ ብርድልብስ እየጣለበት፡፡ አሁን ሲሞቀው ቆሞ መሄድ ይጀምራል” አለ የሱቁ ማናጀር መሆኑን ደረቱ ላይ ከለጠፈው መታወቂያ ላይ አነበብኩ፡፡ ፊትና ኋላው አይለይም ፡፡ እጁን በጀርባው ተንጋሎ ለሚንቀጠቀጠው ሰው ሰጠው፡፡ ሰውየው እጁን በመከራ ይዞ ተነሣ፡፡ ደግፎ ወደ ወንዶች ሱሪ ወሰደው፡፡
“ጉዱንማ ማየት አለብን “ አለች ሴትየዋ ወፈር ደንደን ያለ ከንፈሯን እየላሰች፡፡
ተከተልነው፡፡
“ግን አንቺ ምን አገባሽ አልኳት ድንገት “”
እንደመደንገጥም እንደመሣቅም እያለች “እንዴ ሁኔታውን ለማወቅ ነዋ” አለች በመለማመጥ
ሰውየው ፀይም ረጅም ቀጭን አፍንጫ ሠልካካ መሆኑን ልብ ያልኩት ከቆመ በኋላ ነው፡፡የተሰጠውን ብርድልብስ ወገቡ ላይ አስሮ ከወገቡ በላይ ራቁቱን ሆነ፡፡ የሱቁ ማናጀር ወፍራም ቲሸርት እየመረጠ ሰጠው ሁሉንም እየደራረበ ለበሣቸው ፡፡ ጂንስ ሱሪ ለመምረጥ እጁን ሲዘረጋ ማናጀሩ ከለከለውና ጥቁርና ቢጫ ቱታዎች ሰጠው ፡፡ ሣያመነታ ተቀብሎት ብረቱን ተደግፎ መልበስ ጀመረ ፡፡
እኔም ቤቱ ውስጥ ባለ ሙቀት እጄ ስለተፍታታ ኮዳዬን ከቦርሣዬ መዝዤ መጎንጨት ጀመርኩ፡፡ እንደዚህ ቅዝቃዜ ሲሆን ቀኑ አይሄድም፡፡ ብገዛም ባልገዛም ሱቅ መግባቴ አይቀርም፡፡ ስራ ፈት ነኛ ጊዜው አይሄድልኝም፡፡ እንደመጣሁ የገባሁበት ስራ እረፍት የለውም አስራ ሁለት ሰዓት ሰርቼ በካሽ ገንዘብ አገኛለሁ፡፡ ግን አጎቴን ለመፈለግ እድል አጣሁ፡፡ ሳማክራቸው ለምን ዶ/ሩን ጭንቀት አለብኝ አትይውም አሉኝ፡፡ አልኩት ፃፈልኝ፡፡ በአጭር ጊዜ ከመስራት ወደአለመስራት ተሸጋገርኩ ፡፡ ይኸው አጎቴንም አላገኘሁ እኔም በአእምሮ ህመም ተመዝግቤ ከገባሁበት መውጣት አቅቶኝ በሱስ ተጠምጃለሁ፡፡
“ አየሽው ጉዳችንን ነይ ነይ እይው ሰውየውን “ እያለች ጎትታኝ የወንዶች ጫማ የተደረደረበት ቦታ ወሰደችኝ፡፡
ሰውዬው የተሰጠውን ልብስ ቁጭ ብሎ መቅደድ ጀምሯል፡፡
“እንዴ ከዚህ ሱቅ ሲወጣ ጨካኙ ብርድ እንደሚያቅፈው አያውቅም እንዴ ቀልደኛ”ብዬ ከት ብዬ ሣኩኝ ፡፡ አጠገቤ የነበረችው ሴት “ አይገርምሽም የኛው ነው እኮ የኛው” አለች ድምጿን አጉልታ፡፡
“አልገባኝም “ አልኳት
“ካልገባሽ እኔ ነግርሻለሁ፡፡” አለኝ ደምጹን አጉልቶ ፡፡
ደነገጥኩኝ፡፡ እንግሊዝኛን ከስፓኒሽ ይሁን ከአረቢኛ እየቀላቀለ ማጉረምረም ጀመረ ልብስ መቅደዱን አቁሞ
“ታውቂዋለሽ እንዴ?”አልኳት
“ኧረ እኔ በፍጹም አይኑንና ፀጉሩን አይቼ ነው እንጂ የኛ ነው ያልኩሽ ” አለች ደንግጣ
“በአይንና በፊት እንታወቃለን እንዴ”
“አዎና”አለች ፈርጠም ብላ
“ወሬኛ ቢች ነሽ ቢች ለምን ትፈልጊኛለሽ አሁን የጠራሽውን ትጠሪያለሽ ለሷ የኛ ነው ትያታለሽ በየሄድኩበት የኛው ነው እያላችሁ መድረሻ አሣጣችሁኝ፡፡ ሲበርደኝ አለበሣችሁኝ? ሲርበኝ አጎረሣችሁኝ? የናንተ ሆኜ ምን አደረጋችሁልኝ ?ነውራችሁን በጉያችሁ ሸክፋችሁ የሰው ነውር ላይ ትንሸካሾካላችሁ፡፡ እኔ እንደሁ ብቻዬን መኖር ከጀመርኩ አስራ ሰባት ነው ሃያ ሰባት ዓመት አልፎኛል፡፡ ለበስኩ እራቁቴን ሄድኩ ኖርኩ ሞትኩ ግድ አይሰጠኝም ፡፡ ተውኝ ልኑርበት አልፈልጋችሁም የኛ እያላችሁ አትነካኩኝ” አለ የሰጠውን ቱታ አውልቆ መሬት ጥሎ እንደገና ከመሬት እያነሣ፡፡
“ከሀገር መራቅ ቅጥሙ ይሄ ነው፡፡ በነፃነት ለማበድ አልኩኝ
“ ስሚ ነውርሽን ደብቀሽ ነውሬን ማየት ካማራችሁ የምትገቡበት እስኪጠፋችሁ አከናንባችኋለሁ፡፡” አለና እርቃኑን ቆመ፡፡
አብራኝ የነበረችው ሴት የምትገባበት እስኪጠፋት ደነገጠች ፡፡
መደንገጧን ሲያይ ተበራቶ ወደኛ ቀረበ፡፡ “ ዶንት ተች ሚ አልታየ ይሙት እንዳትነካኝ ” አልኩት ድምፄን አጉልቼ ሰውነቴ እየተርበተበተ፡፡
“አልታየ ሁ ኢዝ አልታየ የኔ ያ የድሮው . . .ሂጂ ከዚህ ከፊቴ ጥፊ የሞተውን እሱን አልታየን ለምን ትጠሩታላችሁ ድሮ ገና እንደመጣ አልችል ብሎ አልቋቋም ብሎ ገንዘቡን ሲወስዱበት እቃውን ሲቀሙት ባቡር ገብቶ ሞቷል፡፡ ገንዘቡን ለኔ ትቶ እኔን መንካት አትችሉም እኔ እንደሱ አይደለሁም ፡፡ አለቃችሁም የነካችሁኝ እናንተ ናችሁ ፡፡ ትከተሉኛላችሁ አንቄ ገልሻለሁ፡፡ ሲጥ አድርጌ “ ብሎ እጁን ከመዘርጋቱ
ማናጀሩና ሁለት ፖሊሶች መሀላችን ገቡ፡፡
test