"ከፈሱ የተጣላ" /ሶስና አሸናፊ/
Edited by : addiskignit@gmail.com -1/5/2023
የሚወርደውን አንሸራታች በረዶ መሬት ሣይደርስ ንፋሱ እየተቀበለ ይረጨዋል። የሚረጨውን በረዶ ከፊታችን ላይ እንዳይደረስ በእጃችን ስንከላከል ንፋሱ እግራችንን ከመሬት ለመንቀል ይታገላል። ቀኑ እንዲህ ነበር ትላንት፣ ትምህርት ቤት ቢዘጋም ስራ ባለመዘጋቱ ሳንወድ በግድ ስራ ገበታችን ላይ ተገኝተናል። ወፍራም ነች! ረዥም። ባደረገችው መነፅር ውስጥ የሚሮጠውን የፍርሀትና የብቸኝነት ስሜት ያየ ሣያናግራት አልፏት ሊሄድ አይችልም።እያንዳንዳችን የስነልቦና ጦርነት ውስጥ ገብተን ነበር የዋልነው። "ቤቴ ሩቅ ነው ምን ላድርግ?" አለች በሚያሳዝንና ግራ በገባው ድምፅ "አንዴ መተሻል እኮ!" አልኳት "የት እንደሆነች ታውቂያለሽ?" አለች ሌላዋ "ቤቷ ለመድረስ አንድ ባቡር ከዚያ ሁለት ባስ ትይዛለች" "ከሁለት ሠአት በላይ ትሄዳለች" ሌላዋ መለሠች። "ሂጂ ንገሪዋ!" አለች አንዷ "አዎን ንገሪው!"ተከተለች ሌላዋ " ምንድነው የሚባለው?" እሷ ጠየቀች "የመጀመሪያ በረዶዬ ነው። ፍርሀት እየናጠኝ ነው። ብለሽ ያለሽን ስሜት ነዋ! የምትናገሪው"አለ ረጅም ቀጭን ሹሩባሙ ልጅ "እንዴ እሱ ምን አገባው ስሜቱ እኮ የሷ ነው" "ታዲያ ምን ትበለው" አልኩ ተናድጄ "ከመጣሁ ሁለት ወሬ ነው ተረብሻለሁ መቋቋም አቅቶኛልነዋ!" ልጅቷ የበለጠ ዞረባት። "አሞኛል ብለሽ ለምን አልደወልሽም?" አልኳት "ፈርቼ ነዋ!" "ምን አስፈራሽ?" " እንዳያባርረኝ" "ለነገሩ እሱ ከፈሱ የተጣላ ነው።እንኳን ይህን አግኝቶ" " የራሱ ጉዳይ" አልኩ ተናድጄ "ዊንተር እኮ ነው ስራ መፈለግ ከባድ ነው ያስጠላል።" አሉ እየተቀባበሉ። " ወጀቡን ለመሸሽ ከቤቴ የወጣሁት 12 ሰአት ነው "አለች ጣልቃ ገብታ አንዷ "ስንት ነበር ምትጀምሪው?" ጠየቀች ሌላዋ "ሁለት ተኩል አሁን አልቻልኩም ደክሞኛል።" አለች ለስራው ክብር አለኝ አይነት ነገር እያሳየች። ሁሉም የየራሡን ጭንቀት መለፍለፉን ቀጠለ። እኔም አልተናገርኩትም እንጂ ሌሊቱን እንቅልፍ በአይኔ አልዞረም። ደግነቱ የቤቴን በር ከፍቼ ስወጣ ውሻቸውን ለማናፈስ ይሁን ለማሣየት ከንፋሱ ጋር እየታገሉ የሚራመዱትንም ሆነ በእድሜ የገፉትንአዛውንቶችን ባላይ የመጀመሪያ እርዳታ ከሚደረግላቸው ውስጥ ነበርኩ። "ምን አለሽ ምን አለሽ?" አሏት ማናጀሩን ጠይቃ ስትመለስ "ነገርኩት"አለች ከእንባዋ ጋር እየታገለች "እና" " ይሄ ካናዳ ነው አለኝ" አለች ከለቅሶ ጋር "ምን" አልኩ ደሜ ፈልቶ "ልክ ነዋ ልክ ነው" አሉ እየተቀባበሉ። ይኸው ነው።. . . ጥለናት ወደ ስራችን ተበታተንን። Storm/ወጀቡ/ አለ ሻማ አዘጋጁ፣ ደረቅ ምግቦች ግዙ ከተባለበት ቀን ጀምሮ የደረሠብን የስነልቦና ጫና ጨርቅ አስጥሎ ያስኬዳል። ዛሬም ማስጠንቀቂያው ቀጥሏል -13 አደገኛ ንፋስ እና ቀላል በረዶ አለ።ንፋሱ ጆሮ ይበጥሳል። ለሠማይ ለምድሩ ያልከበዱትን በአፍጢማቸው ይደፋ። ደግሞ ማን ያውቃል?! ሀገራቸውን ለናፈቁ ንፋሡ እያንከባለለ ሀገራቸው መሬት ላይ ይጥላቸውና ይመሠገን ይሆናል!! ዲሴምበር 24/2022
test